ተደጋግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት እንዴት ተጀመረ?

በ1998 ዓ.ም ተማሪዎች፣ ፕሮፌሰሮች እና ሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲዎች አባላት በዩኒቨርሲቲዎች አርማ ያጌጡ አልባሳት በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስጥ የሰራተኞች መብት እንዳልተከበረ ተገነዘቡ። የኮሌጅ ልብስ ሽያጭ በአሜሪካ ትልቅ ንግድ ነው። በፋብሪካዎች ውስጥ የሠራተኛ መብት ጥሰት ሲታወቅ፣ በኮሌጅ ውስጥም ውጭ ያሉ ብዙ ሰዎች አሳስቧቸው ነበር። ይህንን ችግር ለመከላከል ዩኒቨርሲቲዎቹ የሰራተኞችን መብት በተመለከተ የተወሰኑ መሰረታዊ የደረጃ መመዘኛ ማሟላትን የሚጠይቁ የስነምግባር ደንቦችን ተግባራዊ አድርገዋል። የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የተፈጠረው እነዚህ የስነምግባር ደንቦች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ነው። ዓላማውም ሰራተኞች በፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ ሁኔታዎችን ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ነው። ደንቦቹ እንዲከበሩ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት በፋብሪካዎች ውስጥ የሥራ ሁኔታን የመመርመር፣ የምርመራዎቹን ሪፖርቶች ማተም እና የደንቦች ጥሰቶች በሚገኙበት ጊዜ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ዘዴዎችን የመፈለግ ሃላፊነት አለበት።

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት በአሜሪካ የሰብዓዊ እና የሰራተኞች መብት ባለሙያዎች፣ በዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች እና ተማሪዎች ጥምረት እና በመካከለኛው አሜሪካ እና ኤሲያ ካሉ የሰራተኞች እና የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴ መሪዎች አማካሪነት ነው የተመሰረተው፡፡ የሰብዓዊ እና የሰራተኞች መብት ባለሙያዎችን ያቀፈ አማካሪ ካውንስል የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ከላይ ሆኖ ለመምራት ተቋቁሟል።

 

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ምርመራዎች እንዴት ይተገበራሉ?

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ምርመራዎች ከሰራተኞች ጋር ከፋብሪካው ውጭ፣ በቤት ውስጥ ወይም በአቅራቢያ አካባቢ የሚከናወኑ አጠቃላይ ቃለ-መጠይቆችን ያካትታሉ።  የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ከፋብሪካ አስተዳዳሪዎች፣ ከመንግስት፣ ከክልል ወይም ከፌደራል የሰራተኛ ተቆጣጣሪዎች፣ የሰራተኛ ማህበራት ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የሰራተኛ ጠበቆች እና ሌሎች በክትትል ሂደት ውስጥ ሊረዱ ከሚችሉ ግለሰቦች ጋር በመነጋገር ይሰራል። አስተዳዳሪዎቹ ከፈቀዱ፣ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት በፋብሪካ ውስጥ በመገኘት ፍተሻ ያደርጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ሁሉንም መረጃዎች እና ቃለመጠይቆች ከመረመረ በኋላ የስነምግባር ደንቦችን መከበራቸውን በተመለከተ ውሳኔዎችን ይሰጣል። ጥሰቶች ሲታወቁ፣ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የእርምት እርምጃዎችን ያቀርባል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይፋ የሆነ ዘገባ ታትሟል እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ጥሰቶቹ በተገኙበት ማህበረሰብ ተተርጉሞ ይሰራጫል።

በሥነ ምግባር ደንቦቹ ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን ጉዳዮች በተመለከተ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ለጥቂት ቀናት የሚደረጉ ምርመራዎች በቂ ናቸው ብሎ  የሰራተኛ መብቶች  ጥምረት አያምንም። ለተጨባጭ ምክንያቶች ሲባል፣ በሠራተኞች በራሳቸው ወይም በሌሎች ስለ ፋብሪካው እና ስለ ኢንዱስትሪው እውቀት ባላላቸው ሰዎች ለሚነሱ ጉዳዮች ምርመራ ቅድሚያ ይሰጣል::

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት በሰሜን አሜሪካ የዩኒቨርሲቲዎች የሥነ ምግባር ደንቦች ውስጥ ለተካተቱ ሠራተኞች በመብቶቻቸው ዙሪያ የትምህርት ፕሮግራሞችን ይሰጣል። አላማችን ሰራተኞች የህግ ጥሰት ቅሬታዎችን አገር ውስጥ ላሉ ድርጅቶች እና በተጨማሪም ወደ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ለማቅረብ የሚችሉበትን ምቹ ዘዴ መፍጠር ነው። ማንኛውም ዓይነት ተቆጣጣሪ ድርጅት በዓመት ውስጥ በየቀኑ በእያንዳንዱ ፋብሪካ ውስጥ በመገኘት ክትትል ሊሰራ አይችልም:: በዚህም ምክንያት የሥነ ምግባር ደንብ መከበሩን ለማረጋገጥ የተሻለው መንገድ በየፋብሪካው ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የራሳቸው ተቆጣጣሪ እንዲሆኑ ማሠልጠን እንደሆነ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ያምናል።

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ሙሉ ለሙሉ ለገለልተኛ አካሄድ የተገዛ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም ፍላጎት ያለው ሰው ለሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ልብስ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት እንደ የመረጃ መገኛ ምንጭ አድርጎ መገልገል ይችላል።

 

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ፋብሪካዎቹን ለምርመራ እንዴት ይመርጣል?

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ፋብሪካን የሚመረምረው ከሠራተኛ ቀጥተኛ ቅሬታ ሲደረሰው ወይም ከድርጅቶች በሚመጣ የምርመራ ጥያቄ መሰረት ነው።

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ለሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ልብስ በሚያመርት ፋብሪካ ላይ ከሠራተኛ ቅሬታ ሲደርሰው፣ ይፋዊ ምርመራ ለማድረግ ለመወሰን የሚከተሉትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያስገባል፡- የሠራተኛ መብቶች ጥሰት አሳሳቢነት፣ የአገር ውስጥ ድርጅቶች አስተያየት፣ የቅሬታው ታማኝነት እና ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ የዩኒቨርሲቲዎች ብዛት፣ ማለትም ከየሰራተኛ መብቶች ጥምረት ጋር ዝምድና ያላቸው ምን ያህል ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ፋብሪካ ውስጥ ምርት አላቸው የሚለውን ነው፡፡

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት በተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች ለምሳሌ በፋብሪካ ውስጥ ከባድ ችግር መኖሩን የሚገልጽ ከሀገር በቅል ድርጅት የመጣ መረጃ ካለ፣ አንድ ፋብሪካ በርካታ ምርት ለዩኒቨርስቲዎች እያቀረበ ግን ፋብሪካው ውስጥ ስላለው የስራ ሁኔታ መረጃ በሌለበት ወቅት ወዘት... በቢሮው አነሳሽነት ምርመራ (ማለትም በሶስተኛ ወገን መነሳሳት የማያስፈልጋቸው ምርመራዎችን) ያከናውናል፡፡

 


የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ለአንዳንድ ፋብሪካዎች ትኩረት የሚሰጠው እና ለሌሎች ደግሞ የማይሰጠው ለምንድን ነው?

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት በሁሉም ፋብሪካዎች ውስጥ የሠራተኛ መብቶች እንዲከበሩ ይፈልጋል፤ ነገር ግን ለዩኒቨርሲቲዎች ልብስ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስጥ ብቻ ነው ለውጥን የመጠየቅ እና ጥሰት በሚኖርበት ጊዜ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ የሚችለው። የእኛ ተስፋ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ለዩኒቨርሲቲዎች በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስጥ ሁኔታዎችን ማሻሻል እና እነዚህ ፋብሪካዎች ለሌሎች ፋብሪካዎች ጥሩ ምሳሌ ሆነው ሲያገለግሉ ማየት ነው፡፡

 

ለዩኒቨርሲቲዎች የሚያመርቱት ፋብሪካዎች ዝርዝር ከየት ነው የመጣው?

ከሰራተኛ መብቶች ጥምረት ጋር የተገናኙ ዩኒቨርስቲዎች አቅራቢዎቻቸውን (ከዩኒቨርሲቲው ጋር የዩኒቨርሲቲውን ስም ወይም አርማ የያዘ ልብስ እንዲያመርቱ የተዋዋሉ ኩባንያዎች) ለዩኒቨርሲቲው ምርቶች የሚዘጋጁባቸው ፋብሪካዎችን ዝርዝር እንዲያቀርቡ ይጠይቃሉ። በዚህ መረጃ ላይ በመመስረት፣ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ለዩኒቨርሲቲዎች ልብስ የሚያመርቱ ሁሉንም ፋብሪካዎች ከነ አድራሻቸው የያዘ ሁሉን አቀፍ ዝርዝር ያዘጋጃል።

 

ብራንዶች የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ችግሮች ሲያገኝ ውላቸውን ይሰርዛሉ?

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ሁል ጊዜም ዓለም አቀፍ ኩባንያ በፋብሪካው እንዲቆይ እና ሁኔታዎችን ለማሻሻል ጥረት እንዲያደርግ ይመክራል። የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ውሉን ብቻ አቋርጦ ወደ ሌላ ፋብሪካ የሚሸሽ ኩባንያ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዳልሆነ ያምናል። በሜክሲኮ በሚገኘው የኩክዶንግ ፋብሪካ ጉዳይ በተመለከተ ለምሳሌ፣ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ናይክን በፋብሪካው ውስጥ እንዲቆይ እና ሁኔታዎችን ለማሻሻል እንዲሞክር አስገድዶታል። ናይክ የሰራተኛ መብቶች ጥምረትን ሃሳብ ተቀብሏል።

 

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ምርመራ ውጤቶች ለሕዝብ ይፋ ይደረጋሉ?

አዎ፤ ሁሉም ሪፖርቶች በእንግሊዘኛ የታተሙ ሲሆን አንዳንዶቹ ወደ ሌላ ሀገር ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። ቅሬታዎችን የሚያቀርቡ ወይም በቃለ መጠይቁ ውስጥ የሚሳተፉ ሰራተኞች ማንነት ሙሉ በሙሉ በሚስጥር የተያዘ መሆኑን ማስረገጥ አስፈላጊ ነው::

 

በጣም ብዙ የስነምግባር ደንቦች አሉሠራተኞች እና አጋሮቻቸው በተለያዩ የሥነ ምግባር ደንቦች ስር ያላቸውን መብቶች እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ?

ብዙ ህጎች መኖራቸው እውነት ነው፤ እናም ይሄ ግራ መጋባት ሊያስከትል ይችላል። ግን አብዛኞቹ መመሪያዎች በጣም ተመሳሳይ ናቸው። አብዛኛዎቹ ደንቦች ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ህጎችን እንደ ዋቢ ይወስዳሉ እና ተመሳሳይ የምዘና መለኪያ ደረጃዎችን ያጣቀሱ ናቸው፡- ዝቅተኛ የመነሻ ደመወዝ፣ የስራ ሰዓት፣ የመደራጀት ነፃነት እና የጋራ ውል ስምምነት፣ ኢ-አድልዎዊነት፣ የሴቶች መብት ወዘተ። ብሔራዊ ወይም ዓለም አቀፍ ሕግን፣ ወይም አንድ የተወሰነ የህግ ማእቀፍን ተንተረሶ ማንኛውንም ቅሬታ የሚያቀርብ ሠራተኛ ባብዛኛው ጊዜ ቅሬታው የህግ ተቀባይነትን ያገኛል፡፡

 

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት አስተዳደር ስርዓት እንዴት ነው የተዋቀረው?

 የሰራተኛ መብቶች ጥምረት 18 አባላት ያሉት የዳይሬክተሮች ቦርድ አለው። ይህ ምክር ቤት ስድስት የዩንቨርስቲ አስተዳዳሪዎች ተወካዮች፣ ስድስት የተማሪ ድርጅት ጸረ-ጉልበት ብዝበዛ የተማሪዎች ህብረት (ዩኤስኤኤስ) - United Students Against Sweatshops (USAS) ተወካዮች እና ስድስት የሰራተኛ መብት ተወካዮችን ያካትታል።

 

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ስራ እንዴት ነው በገንዘብ የሚደገፈው?

65% የሚሆነው የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የገንዘብ ድጋፍ ከዩኒቨርሲቲ አጋር ክፍያዎች፣ 25% ከፌዴራል እና ከመሠረት ዕርዳታዎች፣ እና የተቀረው የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የክትትል ስራ ከሚሰራባቸው ግለሰቦች እና ሌሎች አጋሮች የሚገኝ ነው።

 

በየሰራተኛ መብቶች ጥምረት እና በማህበራት መካከል ምን ግንኙነት አለ?

የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የስራ ሁኔታን የሚመረምር እና ሰራተኞችን የማይወክል ድርጅት ነው። የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ሚና ሠራተኞችን የሚወክሉ ማኅበራትን ሚና መተካት አይችልም፣ የለበትምም። የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የሰራተኞች ማህበር የመመስረት እና በጋራ ውል የመደራደር መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ይደግፋል። የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ማህበሮች እውነተኛ እና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት አስፈላጊ መሆናቸውን ይገነዘባል። እንዲሁም፣ የሰራተኛ መብቶች ጥምረት የሰራተኛ ማህበራት ከስራ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ እንደሆኑ ያምናል። የሰራተኛ መብቶች ጥምረት ደቡብ ንፍቀ-ክበብ ከሚገኙ ማህበራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ግንኙነቶችን ለመገንባት ይሰራል።